2 Kings 21

የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ

21፥1-10 ተጓ ምብ – 2ዜና 33፥1-10 21፥17-18 ተጓ ምብ – 2ዜና 33፥18-20 1ምናሴ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አምሳ አምስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሐፍሴባ ትባል ነበር። 2ምናሴ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳድዶ ያወጣቸውን የአሕዛብን አስጸያፊ ልማድ በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 3አባቱ ሕዝቅያስ ያፈረሰውን የየኰረብታውን ማምለኪያ ስፍራ መልሶ ሠራ፤ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም ለበኣል መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ምስል ዐምድ ሠራ። እንዲሁም ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም። 4እግዚአብሔር፣ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያዎችን ሠራ። 5በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ መሠዊያ ሠራ። 6የገዛ ልጁን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ
ወይም፣ የራሱን ልጅ በዚህ ውስጥ እንዲያልፍ አደረገ።
፤ መተተኛና ጠንቋይ ሆነ፤ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ምክር ጠየቀ፤ እግዚአብሔርን ለቍጣ የሚያነሣሣውን ክፉ ድርጊት በፊቱ ፈጸመ።

7የሠራውን የአሼራን የተቀረጸ ምስል ዐምድ ወስዶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አስቀመጠ፤ ይህም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፣ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ” ያለው ስፍራ ነው። 8እንዲሁም፣ “ብቻ ያዘዝኋቸውን ሁሉ ተጠንቅቀው በመፈጸምና ባሪያዬ ሙሴ የሰጣቸውንም ሕግ በሙሉ በመጠበቅ ይጽኑ እንጂ ከእንግዲህ የእስራኤላውያን እግር፣ ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር ወጥቶ እንዲንከራተት አላደርግም” ያለው ስለዚሁ ስፍራ ነው። 9ሕዝቡ ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ ይልቅ ክፉ ድርጊት እንዲፈጽሙ ምናሴ አሳታቸው።

10 እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፤ 11“የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አስጸያፊ ኀጢአት ሠርቷል፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩት አሞራውያን ይልቅ ክፉ ድርጊት ፈጽሟል፤ ይሁዳንም በጣዖታቱ አስቷል። 12ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ለሚሰማ ሁሉ ጆሮዎቹ ጭው እንዲሉ የሚያደርግ ክፉ መከራ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ። 13በሰማርያ ላይ ያዘጋጀሁትን መለኪያ ገመድ፣ የአክዓብንም ቤት የለካሁበትን ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤ አንድ ሰው ሳሕን እንደሚወለውል ከወለወለም በኋላ እንደሚገለብጠው እኔም ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ። 14የርስቴንም ቅሬታ እተዋቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ብዝበዛና ምርኮ ይሆናሉ። 15ይህን የማደርገውም የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ድርጊት ስለ ፈጸሙና ለቍጣ ስላነሣሡኝ ነው።’ ” 16ይልቁንም ምናሴ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት እንዲፈጽም ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ፣ ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር እስኪሞላት ድረስ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።

17በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የሠራውን ኀጢአት ጨምሮ የፈጸመው ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 18ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ “የዖዛ አትክልት” በሚባለው በቤተ መንግሥቱ አትክልት ውስጥ ተቀበረ። ልጁ አሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ አሞን

21፥19-24 ተጓ ምብ – 2ዜና 33፥21-25 19አሞን ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ሜሶላም ትባላለች፤ እርሷም የዮጥባ አገር ሰው የሐሩስ ልጅ ነበረች። 20አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 21አባቱ በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ አባቱ ያመለካቸውን አማልክት አመለከ፤ ሰገደላቸውም። 22የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፤ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም።

23የአሞንም ሹማምት ዐመፁ፤ ንጉሡንም በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት። 24ከዚያም የአገሩ ሕዝብ በንጉሥ አሞን ላይ ያመፁትን ሁሉ ገደሉ፤ ልጁን ኢዮስያስንም በእግሩ ተክተው አነገሡት።

25በአሞን ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 26እርሱም በዖዛ አትክልት ውስጥ ባለው መቃብሩ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

Copyright information for AmhNASV